best host for bands

ከደቡብ እስከ ኦሮሚያ የዘለቀው የሙስና ወንጀል….

ወጣትነት እራሳችንን ፈልገን ለማግኘት የምንተጋበት ፣ መክሊቴ ምን ይሆን ? ብለን እራሳችንን በአግባቡ ጠይቀን ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት የምንጥርበት ፣ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ጠቃሚ ሥራ ሰርተን ለማለፍ የሚረዳን እና መሰረት የምንጥልበት የዕድሜያችን አንዱ ክፍል ነው፡፡

 ውድ አንባቢዎቻችን ከላይ እንደ መንደርደሪያ ያስቀመጥነውን ርዕሰ ጉዳይ ያነሳነው ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖበት ለሀገሩና ለወገኑ ብዙ ይሰራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ወጣት የሕዝብን አደራ ወደ ጎን በመተው በተሰጠው የሥራ ሀላፊነት የመንግስትና የሕዝብን ሀብት በመመዝበር ከራሱ አልፎ ሙሉ ቤተሰቡን ጠራርጎ ወደ እስር ቤት ያስገባ በአንድ ወጣት አስተባባሪነት ስለተፈፀመ የሙስና ወንጀል ልናወጋችሁ ስለወደድን ነው፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፤ አቶ ቢኒያም አካለ የ24 ዓመት ወጣት ሲሆን በ2002 ዓ/ም ከአዳማ ዩንቨርስቲ በአካውንቲንግ ተመርቆ በሲልጤ ዞን ሲልጤ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት የክፍያ እና ንብረት አስተዳደር ኦፊሰር ሆኖ የመንግስትን ሥራ ተቀላቀለ፡፡

በዚሁ ጊዜ ነበር የወንጀሉ መሪ ተዋናይ ሆና በዚህ በምናወጋችሁ የሙስና ወንጀል መረብ ውስጥ ተሳታፊ ከሆነችውና በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የአይ.ሲ.ቲ መምህርት ከሆነችው ከሕይወት አዳነ ጋር የተዋወቀው፡፡ ጊዜ ሳያጠፉም በ2006 ዓ/ም የአገሬውን ሕዝብ ጉድ ያሰኘ የጋብቻቸው የመልስ ድግስ ተደግሶ ጋብቻቸውን ፈጸሙ፡፡ ያካባቢው ማህበረሰብ በአቶ ቢኒያም አኗኗር ላይ ጥርጣሬ ማሳየት የጀመረው በዚህ ወቅት ነበር፡፡ አቶ ቢኒያም የ2628 ብር ደመወዝተኛ ሆኖ ሳለ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ብዙ ወጪ የወጣበት የመልስ ድግስ ሊያስደግስ ቻለ ? በሚል፡፡

አንደኛ ተከሳሽ አቶ ቢኒያም በሲልጢ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ዋና ሥራው የነበረው የገጠር መምህራንን ደሞዝ መክፈል ነበርና መቼም የሥነ-ምግባር ደሀ ሆኖ አንዴ በመፈጠሩ የክቡር ሙያ ባለቤት የሆኑትን መምህራንን ማመናጨቅና መሳደቡን ሥራዬ ብሎ ተያያዘው፡፡ የመምህራኑ ጥርጣሬና ተቃውሞ እየበረታ ሲመጣ ጽ/ቤቱ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ ፡፡ መምህራኑ ዘንድ በአካል መሄዱ ቀርቶ ቢሮው ቁጭ ብሎ¡ የወረዳው መንግሥት ሰራተኞችን ደመወዝ በየወሩ ወደ ባንክ እንዲያስተላልፍ ተመደበ ፡፡

"ለሆዳም በሬ……." እንዲሉ በዚህ ወቅት ነበር አቶ ቢኒያም የሌብነት መረቡን እንዴት መዘርጋት እንዳለበት ዕቅድ አውጥቶ ወደ ተግባር የገባው፡፡ የኃላፊን ፊርማ በተለያየ መንገድ እየተጠቀመ በአራት ወራት ውስጥ የ56 ሰራተኞች ዝርዝር በማዘጋጀትና ለያንዳንዳቸው የባንክ አካውንት ቁጥር በመጥቀስ 150.000 ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

ዝርዝሩ የተላለፈለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅበት ቅርንጫፍ ሁለት ጊዜ ፔሮል ተዘጋጅቶ የደመወዝ ጥያቄ የመተላለፉ ነገር ጥርጣሬ ውስጥ ስለከተተው የስልጢ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤትን ሂደቱ እንዴት እንደሆነ ይጠይቃል፡፡ ጽ/ቤቱም ዝርዝሩን ወስዶ ሲያጣራ 56ቱ ግለሰቦች የራሱ ሠራተኞች እንዳልሆኑ ያረጋግጣል፡፡

የማጭበርበር ወንጀል እንደተሠራ ያረጋገጠው ጽ/ቤት ጉዳዩን ለፖሊስ ያሳውቃል፡፡ ተከሳሽ ድርጊቱ በእርሱ ተፈፅሞ እንደሆነ እርግጠኛ ለመሆን በስልክ ሲጠየቅ ወንጀል መፈፀሙን በሚገባ ያወቀው ተከሳሽ ቢኒያም ቤተሰቦቹ ጋር በመጣበት የዕረፍት ቀኑ የፈፀመው የሙስና ወንጀል እየተደረሰበት መሆኑን በሚገባ ስላወቀ ወደ ወረዳው ብሄድ አይመልሰኝ በሚል አቶ ቢኒያም 120 ሺህ ብር ይዞ ከአካባቢው ይሰወራል፡፡

 የአቶ ቢኒያምን መሰወር ያረጋገጠው የሲልጤ ዞን ፖሊስ ጊዜ ሳያጠፋ ወደ ምርመራ ይገባል፡፡ ነገር ግን የወንጀሉን ክብደትና ውስብስብነት የተረዳው የወረዳው ፖሊስ የክልሉ የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በምርመራ እንዲያግዘው ትብብር ይጠይቃል፡፡ በዚህም አግባብ ሁለቱ የፍትህ አካላት በጋራ ምርመራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

የክልሉ የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ያሰማራው ቡድን ከፖሊስ ጋር በመሆን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተከሳሹ የአቶ ቢኒያም ቤት ሲበረበር ባንክ በየግለሰቦቹ ስም ገንዘብ ሲልክበት የቆየባቸውን ቀሪ ደረሰኞችና የሰዎችን ስም ዝርዝር የያዘ ሰነድ ማግኘት ቻለ፡፡

ውድ አንባቢዎቻችን መቼም ለሙስና ወንጀል መፈፀም ዋናው ምክንያት የሥነ-ምግባር ዝቅጠትና የግለሰቦች የስግብግብነት ባህሪ ነውና አቶ ቢኒያም እራሱ በስሙ የሚዘርፈው ገንዘብ አላረካ ስላለው ባንክ ገንዘብ ገቢ ከሚደረግላቸው ግለሰቦች ውስጥ የእናቱ፣ የአባቱ፣ የሁለት እህቶቹ፣ የባለቤቱ እናት እና የባለቤቱን እህት ስም ተጠቅሞ የሕብረት ሥራ ሠራተኛ፣ የማዘጋጃ ቤት ሠራተኛና የፋይናንስ ሠራተኛ እንደሆኑ በሚገልፅ መረጃ እሱ ባዘጋጀላቸው የባንክ ሂሳብ ገንዘቡ ገቢ እየተደረገ ምዝበራውን አጧጡፎት መቆየቱን በብርበራ ወቅት ከተገኘው መረጃ ማረጋገጥ ተቻለ፡፡ ከቤተሰቡ ውጪ ያሉትንና በዝርዝሩ ውስጥ ስማቸው የተካተቱትን ግለሰቦች እንዴት አገኛቸው? ለየግለሰቦቸ የአካውንት ቁጥር እንዴት አገኘ? የሚለው ሌላው የመርማሪ ቡድኑ የምርመራ አቅጣጫ ያተኮረበት ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ይሄን ሰፊ የዘረፋ ተግባር ሲፈፅም እጅግ ተደራጅቶ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እነዚህን ግለሰቦች የሚመለምሉለትን አቶ ከድር ሁሴን እና ዳውድ ደሌ ሦስተኛና አራተኛ ተከሳሾችን ሻሸመኔ ላይ ሰዎችን እንዲመለምሉለት በማሰማራት፣ ሲልጢ ወረዳ ግብርና ሠራተኛ የሆነው 14ተኛ ተከሳሽ አብዴታ ጉደታ ወራቤና ዝዋይ ላይ፣ ስራ አጥ የሆነው አምስተኛ ተከሳሻ በረከት አካለ ቡታጅራ ላይ እየመለመለ- እሱ ሥራ አጥ ሆኖ ሳለ ደሞዝ ይከፈለው እንደነበር በምርመራው ወቅት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከድር ሁሴን በሻሸመኔ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ የሚሰራ ወጣት ሲሆን ዳውድ ደሌ ደግሞ የሻሸመኔ የመሰናዶ ት/ቤት አስተማሪ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በምርመራው ማረጋገጥ እንደተቻለው ከድር በስሙ ስድስት አካውንት፣ ዳውድ በስሙ አምስት አካውንት ያላቸው ሲሆኑ በእያንዳንዱ አካውንት ገንዘብ ይተላለፍልቸው ነበር፡፡ መርማሪ ቡድኑ የአካውንት ቁጥሮቹ እንዴት እንደተገኙ ባደረገው ማጣራት አንደኛ ተከሳሽ ከድር ነጋዴዎችን ዳውድ ደግሞ ተማሪዎችን እንዲመለምል በማሰማራት የአካውንት ቁጥራቸውን ለማግኘት ቤተሰብ ገንዘብ ልኮልን መታወቂያችን ያልታደሰ በመሆኑ ማውጣት ስላልቻልን የናንተን አካውንት እንጠቀም በሚል ማጭበርበር የአካውንት ቁጥር ይወስዳሉ፡፡ ቁጥሩንም ወስደው ለቢኒያም ያስተላልፋሉ እርሱ ደግሞ እንደ አንድ ሰራተኛ አድርጎ ለባንክ ያስተላልፋል፡፡ ሌላዋ ግለሰቦችን መልማይ ስድስተኛ ተከሳሽ ሆና በነቢኒያም የክስ መዝገብ የቀረበችው አመልማል በለጠ የቢኒያም የቅርብ ወዳጅና የሥራ ባልደረባ ናት፡፡ ይህች ሴት ደግሞ በወንጀሉ እንዴት ተሳታፊ እንደሆነች በተደረገው ማጣራት ሰዎችን ከመመልመል በተጨማሪ ግለሰቧ ስልጠና ሳትሄድ ስልጠና እንደሄደች ተደርጎ ገንዘብ እየፈረመች ትቀበል እንደነበር በማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ውድ አንባቢዎቻችን መርማሪ ቡድኑ ሌት ተቀን ሳይል የዚህን ውስብስብ የሙስና ወንጀል ዱካ መከተሉን ቀጥሏል፡፡ መረጃን መረጃ እየወለደ አንደኛ ተከሳሽ 700 ሺህ ብር በሚስቱ እህት አካውንት ማስተላለፉን የሚያሳይ መረጃ በመርማሪ ቡድኑ እጅ ገባ፡፡ መርማሪ ቡድኑ ጊዜ ማባከን ሳያስፈልገው በፍጥነት ግለሰቧን በቁጥጥር ሥር እንድትውል ማድረግ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ደረሰ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ግለሰቧ እናቷ እና እህቷ ስለታሰሩ እነሱን ለመጠየቅ ወደ ቅበት ዘልቃ ነበርና ያለምንም እንግልት እርሷን በቁጥጥር ሥር በማድረግ ምርመራው ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ በግለሰቧ ላይ ምርመራው ተጠናክሮ ሲቀጥል 700 ሺህ ብር በሻሸመኔ ዳሽን አባሮ ቅርንጫፍ በስሟ እንዳለ መረጃ ሰጠች፡፡ ይሄን ገንዘብ የምታስቀምጠው በስሟ ቢሆንም ገንዘቡ የራሷ እንዳልሆነና ለአንደኛ ተከሳሽ ለቢኒያም በአደራ እንዳስቀመጠች፤ ነገር ግን አሁን የግለሰቡን በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በሕግ እየተፈለገ መሆኑን ስትሰማ ይሄም ገንዘብ በወንጀል የተገኘ ይሆናል በሚል ጥርጣሬና ዳፋው ለኔ ቢተርፍስ በሚል ስጋት በባለቤቷ አባት ወይም በአማቿ ስም ገንዘቡን ባንክ ማስገባቷን ለመርማሪ ቡድኑ ቃልዋን ሰጠች፡፡ ለመሆኑ ይሄ ገንዘብ ግለሰቧ በሰጠችው ቃል መሰረት በተባለበት ቦታ አለ? ቀጥሎ መርማሪ ቡድኑ ለማረጋገጥ የተንቀሳቀሰበት ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ቡድኑ ግለሰቧን በመያዝ ወደ ሻሸመኔ በመንቀሳቀስ ገንዘቡ ተቀምጦበታል ወደተባለበት ባንክ አቀና፡፡ የሻሸመኔ ዳሽን ባንክ አባሮ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅን ከየት እንደመጡና ምን ፈልገው እንደመጡ በመግለፅ የባንክ ስቴትመንት ኮፒ ተረርጎ እንዲሰጠው ቡድኑ ይጠይቃል፡፡ በአማቿ በተከፈተው አካውንት 700 ሺህ ብር እንዳለ ተረጋግጦ ብዙም ሳይቆይ ፕሪንት ሲደረግ 550 ሺህ ብር ወጪ መደረጉ ታወቀ፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ የሆነ መደናገጥና መረበሽ በሥራ አስኪያጁ ላይ ታየ፡፡ ምን እንደተከሰተ በተደረገው ማጣራት ከሌላው የዳሽን ባንክ ቅርንጫፍ ማለትም አቦስቶ ዳሽን ባንክ ገንዘቡ ከተወሰኑ ሰኮንዶች በፊት ወጪ እንደሆነ ለማወቅ ተቻለ፡፡ መርማሪ ቡድኑ አንደኛው ዐቃቤ ሕግ በፍተሻ ወቅት ለባንኩ ዘበኞች ያስረከበውን ትጥቅ እንኳን ለመረከብ ጊዜ ሳያጠፋ በብርሃን ፍጥነት ወደ ተባለበት ቅርንጫፍ ባንክ ከነፉ፡፡ ነገር ግን ባንኩ ዘንድ ሲደረስ ገንዘቡ ከጥቂት ሰኮንዶች በፊት ወጪ መደረጉን ወጪ ያደረጉት ግለሰቦች ገንዘቡን በመያዝ ወደ ቤታቸው እንደተመለሱ ተገለፀ ፡፡ ለመርማሪ ቡድኑ ሌላ ነገር ነው የተከሰተው ፡፡ ቢሆንም በዝምታ መታለፍ የማይቻል በመሆኑ ቀጣይ እርምጃ ወደ ግለሰቡ ቤት ማምራት በመሆኑ አሁንም በፍጥነት ወደ ግለሰቦቹ ቤት ቡድኑ ያመራል ፡፡ መርማሪ ቡድኑ ልክ ከቤቱ በራፍ ሲደርስ እና ግለሰቡ ገንዘቡን ይዞ ሲገባ አንድ ይሆናል፡፡ ባለቤታቸው ሊያነጋግሯቸው የቤቱን በራፍ ከፍተው ሲወጡ አሁን የገቡትን ባለቤቶን ማናገር እንፈልጋለን ሲሉ በትህትና ይጠይቃሉ፡፡ሽማግሌው ከውስጥ ሲወጡና መርማሪዎቹን ሲያነጋግሩ የመርማሪዎቹን ቀልብ የሚስብ አንድ ሁኔታ ተፈጠረ- ግለሰቡ በሱሪያቸው አራቱም ኪሶች አስር አስር ሺህ ብር 40 ሺህ ብር ይዘው ነበር፡፡ የመጀመሪያው የመርማሪዎቹ ጥያቄ ወደ አንደኛ ተከሳሽ ሚስት እህት በመጠቆም ይህችን ሴት ያውቋታል? የሚል ነበር፡፡ ግለሰቡም ሲመልሱ አዎ! የልጄ ባለቤት ናት አሉ፡፡ የሕግ አካሎች ነን ብለው ለአዛውንቱ ለማስረዳት ቢሞክሩም ግለሰቡ መጥሪያ ካላመጣችሁ በማለት ከመርማሪዎቹ ጋር ንትርክ ይገጥማሉ፡፡ መርማሪዎቹ በጥብቅ ዲስፕሊን የሰውዬውን ቁጣ ለማብረድ መታወቂያ በማሳየት የሕግ አካል እንደሆኑ ገለፁ፡፡ ግለሰቡ ግን የፈፀሙት ተግባር ያሸማቃቸው ወይም በትክክል ፍትህ ያጣ አካል ሆነው ለመገኘት በአካባቢው ተሰብስቦ ሁኔታውን ሲታዘብ የነበረውን ሕዝብ ማነሳሳት ጀመሩ፡፡ ዝም ብላችሁ ታያላችሁ? እነዚህ ሕገ ወጥ ሰዎች ናቸው፡፡ ከሌላ ክልል በመምጣት ያለአግባብ ሊወነጅሉኝ እየሞከሩ ነው በማለት ታገሉ፤ ቤት ገብቼ ልውጣ ሲሉም በቁጣ ጠየቁ፤ ከምርመራ ቡድኑ ወደ ቤታቸው አምልጠው ለመግባትም ሙከራ አደረጉ፤ ነገር ግን ይሄ ሁሉ አልተሳካላቸውም፡፡ በዚህ አላበቁም እኝሁ ግለሰብ አርባ ሺህ ብሩን የሰጠ

ጎረቤቴ ነው ግብር ክፈልልኝ ብሎ የሚል ቅጥፈት አመጡ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ብሩን ሰጠኝ ያሉት ግለሰብ በአቅራቢያው ነበርና እንካ ብርህን ሲሉ ሙግት ገጠሙት፡፡ ግለሰቡ ግን ያለውን ሁኔታ ሲረዳና እየተከናወነ ያለው ነገር ወንጀል መሆኑን ስላወቀ ሽማግሌው የፈጠሩትን ድራማ በአግባቡ ሊተውንላቸው አልቻለም፡፡

በመጨረሻም በየትኛውም መንገድ ሊሳካላቸው አለመቻሉን የተረዱት ግለሰቡ ወደ ቤት ገብተን እንነጋገር የሚለውን ሀሳብ ተቀበሉ፡፡ መርማሪ ቡድኑ ከሻሸመኔ ፖሊስ አባላት ጋር በመሆን ወደ ቤት ሲዘልቁ ቀሪው ገንዘብ በሻንጣ ተቀምጦ አገኙት፡፡ ግለሰቡ ወደ ቤት ገብተው ቁጭ ካሉና መረጋጋት እንደጀመሩ ለልጃቸው ሚስት ጥያቄ ሰነዘሩ- ልጄ እነዚህን ሰዎች ይዘሽብኝ የመጣሽው አንቺ ነሽ? ታውቂያቸዋለሽ ? ሲሉ፡፡ ልጅቷም አዎ! አባባ ስትል ምላሽ ሰጠቻቸው፡፡ ቀጠሉና ለመርማሪ ቡድኑ ጥያቄ ሰነዘሩ ከኔ ምንድን ነው የምትፈልጉት? ሲሉ፡፡ ቡድኑም ከሳቸው ገንዘቡን እንደሚፈልግ ግልፅ አደረገላቸው፡፡ አዛውንቱም በሻንጣ ሞልተው ከባንክ ያመጡትን 550 ሺህ ብር አስረከቡ፡፡ ገንዘቡን ከግለሰቡ ከተረከቡ በኋላ እንዴት እናድርገው የሚለው ጥያቄ ቡድኑን ብዙ ካከራከረ በኋላ ወደ ወጣበት ባንክ ይመለስ የሚለው ሀሳብ ሚዛን ስለደፋ ገንዘቡን ይዘው ወደዛው በማምራት በሲልጤ ዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ዝግ አካውንት ገንዘቡ እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡

ይሄ የሙስና ወንጀል መረቡ የሰፋ ነው የሚለው ጥርጣሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለበት የመጣው የምርመራ ቡድን ይሄ ግለሰብ ሌላም የዘረፈው ነገር አይታጣም በሚል ማረሚያ ቤት በሚገኙት ቤተሰቦቹ ላይ ምርመራውን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ልጅ ሻሸመኔ ላይ ቤት አለው አይደል? መርማሪው ለአንደኛ ተከሳሽ እናት ጥያቄ አቀረበ፡፡ እናት ሲመልሱ አዎ! በታናሽ እህቱ በሴት ልጄ ስም አለው አሉ፡፡ በስሟ ቤት የተሠራላት የአንደኛ ተከሳሽ እህት የ17 ዓመት ታዳጊና የመሰናዶ ት/ቤት ተማሪ ናት፡፡ መርማሪ ቡድኑ ጠርቶ ሲጠይቃት በሻሸመኔ 05 ቀበሌ ልዩ ስሙ ቡልቻና በሚባለው አካባቢ ሰርቪስ ቤት እንደሰራላት ተናገረች፡፡ ቡድኑም ማዘጋጃ ቤት በመሄድ በስሟ ካርታ እንደተሠራ አረጋግጦ ካርታውን ኮፒ አድርጎ ወሰደ፡፡ በመቀጠል የተባለው ሰርቪስ ቤት በእርግጥ ሰርቪስ ቤት መሆኑን ለማረጋገጥ ሲኬድ ደረጃውን የጠበቀ ቪላ ቤት ሆኖ ተገኘ ፡

ከዚህ በኋላ ሀዋሳ በመምጣት ከክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የማገጃ ትዕዛዝ በመውሰድ ቤቱ እንዲታገድ ተደረገ፡፡ የፅሁፋችን አንባቢዎች ይሄ ሁሉ የምርመራ ሂደት ተካሂዶ በሙስና ወንጀሉ በርካታ ገንዘብ በአንደኛ ተከሳሽ ቡድን መሪነት እንደተመዘበረና ለግል ጥቅም እንደዋለ ከላይ በሰፊው አስቃኘናችሁ፡፡

ይሁን እንጂ ከላይ ባስቀመጥንላችሁ የገንዘብ መጠን ብቻ ይሄ ሁሉ ሀብት ሊኖር እንደማይችል ግምት መውሰዳችሁ አይቀሬ ነውና እስቲ አሁን ደግሞ አንደኛ ተከሳሽ ቢኒያም እንደ ገንዘብ ማግኛ ምንጭ ይጠቀምባቸው የነበሩና መርማሪ ቡድኑ በማጣራት ሂደት የደረሰባቸው እውነታዎችን እናካፍላችሁ፡፡ አሁንም አብራችሁን ቆዩ፡፡

ቢኒያም የገጠር መምህራን ደመወዝ ከፋይ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መርማሪው ቡድን ወደ ቅበት ከተማ በማምራት በፔሮል ላይ ባደረገው ማጣራት በሞተ ሰው ስም፣ ከነጭራሹም መኖሩም በማይታወቅ ሰው ስም ፔርል እያዘጋጀ፣ እራሱ እየፈረመ ሀላፊዎችን እያስፈረመ ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ መዝብሯል፡፡ እንደዚሁ በዚሁ ክስ መዝገብ ተከሳሽ ሆነው ከቀረቡ ሀላፊዎች ጋር በመመሳጠር ምንም ስልጠና ሳይኖር ስም ዝርዝር በማዘጋጀት፣ ፊርማዎችን በመፈረም ገንዘብ ይመዘብር እንደነበር በማስረጃ ሊረጋገጥ ችሏል፡፡ የዚሁ ዘረፋ ውጤት የሆነ 900 ሺህ ብር በሚስቱ እናት ስም ያንቀሳቀሰ መሆኑን የሚጠቁም መረጃም በመርማሪ ቡድኑ እጅ ገባ፡፡ ውድ አንባቢዎቻችን በክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ፣ በሲልጤ ዞን ፖሊስ ቅንጅታዊ ሥራ እንደዚሁም በሻሸመኔ ከተማ ፖሊስና ነዋሪ ሕዝብ ትብብር ከአንድ ዓመት እልህ አስጨራ

የምርመራ ሥራ በኋላ ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ በቃ፡፡ የካቲት 24/ 2008 ዓ/ም የስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማለዳ ችሎት ተሰይሟል፡፡ በነቢኒያም አካለ ካሳ የክስ መዝገብ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት 14 ተከሳሾች በክስ መዝገቡ ተጠያቂ ተደረጉ፡፡ በዚህም መሰረት አንደኛ ተከሳሽ ቢኒያም አካለ ካሳ 25 ዓመት ፅኑ እስራትና 105‚000 የገንዘብ መቀጮ፣ 2ተኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሕይወት አዳነ ተፈሪ ከላይ እንደገለፅንላችሁ የአንደኛ ተከሳሽ ባለቤት ስትሆን በ14 ዓመት ፅኑ እስራትና በ50‚000 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ፣ ሦስተኛ ተከሳሽ ሁሴን ከድር ቻንቹ በ10 ዓመት ፅኑ እስራትና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ፣ አራተኛ ተከሳሽ ዳውድ ዶሌ ክሮርሶ በ10 ዓመት ፅኑ እስራትና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተቀጥተዋል፡፡ ውድ አንባቢዎቻችን ይሄንን የሙስና ወንጀል ልዩ ያደረገውና እጅን ባፍ ያስጫነው ጉዳይ የወንጀሉ መሪ ተዋናይ የሆነው የአንደኛ ተከሳሽ ቤተሰቦች ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ የወንጀሉ ተሳታፊ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ በዚህም መሠረት የአንደኛ ተከሳሽ ወንድም የሆነው በረከት አካለ ካሳ አምስተኛ ተከሳሽ ሲሆን ስድስት ዓመት ፅኑ እስራትና 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ፣ ወ/ሮ በቀለች ረጋ የአንደኛ ተከሳሽ ሚስት እናት ስትሆን በ3 ዓመት ፅኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ፍ/ቤቱ ወስኗል፡፡ ባጠቃላይ በዚህ የሙስና ወንጀል የተሳተፉት 14 ግለሰቦች ሲሆኑ ሁሉም ፍ/ቤት ገብተው በፈፀሙት የሙስና ወንጀል መጠን ተገቢ ቅጣታቸውን ተቀብለዋል፡፡